ለአበባ አትክልትና ፍራፍሬ የሚሆኑ ተጨማሪ ቦታዎች እየተዘጋጁ ነው
የብድር ማራዘሚያ ዕድሉ 30 ኩባንያዎችን ከመሸጥ እንዳዳናቸው ተገለጸ
በዳዊት ታዬ
ከአበባ፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ ምርት የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ የሚያስችል ተጨማሪ የመሬት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡
‹‹ሆርቲ ፍሎራ ኢትዮጵያ 2011›› በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት አስመልክቶ የኢትዮጵያ አበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና ላኪዎች ሊቀመንበር አቶ ፀጋዬ አበበ እንደገለጹት፣ መንግሥት ከአምስት እስከ ሰባት ሺሕ ሔክታር የሚሆን መሬት ይዘጋጃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሁሉም ክልሎች ለአበባ አትክልትና ፍራፍሬ ሊሆኑ የሚችሉ ቦታዎች ተመርጠው ወደ መሬት ባንክ እየገቡ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ፀጋዬ፣ ተጨማሪ ቦታዎች ማዘጋጀት በዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡
በአሁኑ ወቅት በአበባ እርሻ የተሸፈነው መሬት ከ1,600 ሔክታር የማይበልጥ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ፀጋዬ፣ በቀጣይ ዓመታት ይህ ከእጥፍ በላይ ያድጋል፡፡
ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የአትክልትና ፍራፍሬ የሚመረትበትም የመሬት ይዞታ ከአንድ ሺሕ ሔክታር መሬት በታች በመሆኑ ተጨማሪ ቦታዎችን ማዘጋጀቱ የአትክልት ፍራፍሬ ምርት እንዲያድግ እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል፡፡
እስካሁን ባለው መረጃም በአበባ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ ያሉ ኩባንያዎች በተረከቡበት ቦታ ላይ ሙሉ ለሙሉ እያለሙ ከሆነ ተጨማሪ ቦታ የማግኘት ዕድል እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡
የአበባ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት እያስገኘ ያለው ጠቀሜታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ በየዓመቱ ከ25 እስከ 30 በመቶ ዕድገት እያሳየም ነው ተብሏል፡፡ ባሳለፍነው ረቡዕ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በይፋ የተከፈተው የንግድ ትርዒት ላይ እንደተገለጸውም፣ መንግሥት በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የሰጠውን ብድር የመክፈያ ጊዜ ማራዘሙ ከ30 የሚያንሱ የአበባ እርሻዎች ከሽያጭ እንዲድኑ አድርጓል፡፡ የአበባ እርሻዎቹ የብድር ጊዜን ማራዘሚያ ማግኘታቸው ደግሞ የበለጠ እንዲሠሩ አበረታቷቸዋል፡፡
ከአበባ የወጪ ንግድ በዓመት እየተገኘ ያለው ገቢ ወደ 160 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ከአትክልትና ፍራፍሬ የወጪ ንግድ ደግሞ በአሁኑ ወቅት እየተገኘ ያለው ዓመታዊ ገቢ ከ40 ሚሊዮን ዶላር ያልበለጠ ነው፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት ማጠቃለያ ላይም ከአበባ 190 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እንደ አቶ ፀጋዬ ገለጻ፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የሚያስችል ስትራቴጂ ተነድፏል፡፡ ከአትክልትና ፍራፍሬ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ከእጥፍ በላይ ማሳደግ የሚቻልበት የአየር ንብረት፣ የሰው ኃይል የማልሚያ ቦታዎችና ለምርቱ ዕድገት ጠቃሚ ግብዓቶችን በቀላሉ ማግኘት የሚችል በመሆኑ በቀጣይ ዓመታት ከአትክልትና ፍራፍሬ የሚገኘው ገቢ እንደሚጨምርም ገልጸዋል፡፡
አበባም ሆነ አትክልትና ፍራፍሬን አሁን ከሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ከእጥፍ በላይ ለማሳደግም ወደ ውጭ የሚላከውን ምርት በአውሮፕላን ብቻ በመላክ እንደማይሆን ጠቁመዋል፡፡
ምርቶቻችንን በአውሮፕላን በመላክ ብቻ ተወዳዳሪ መሆን አንችልም ያሉት አቶ ፀጋዬ፣ የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርት በባሕር ትራንስፖርት ጭምር መላክ ይኖርበታል፡፡ አትክልትና ፍራፍሬ በመላክ የሚታወቁ እንደ ሞሮኮ፣ ግብፅ የመሳሰሉ አገሮች በዚህ ተጠቃሚ እየሆኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ በአበባ አምራችነቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነችው ኬንያ እንኳን በአየር ትራንስፖርት ከምትልከው ምርቷ ያልተናነሰ በመርከብ ትልካለች፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ግን እንዲህ ዓይነት አገልግሎት ባለመጀመሩ ተወዳዳሪነት ላይ ተጽዕኖ አሳርፏል፡፡ ስለዚህ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ትኩረት እንዲሰጥበትም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡
ባሳለፍነው ረቡዕ በተከፈተው ኤግዚቢሽን ላይ ከ24 አገሮች የተውጣጡ 120 የሚሆኑ ኩባንያዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ 41 የሚሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ የአትክልትና ፍራፍሬ ገዢዎችም ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ኤግዚቢሽኑን የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከሁለት ሰዓታት በላይ ጊዜ ወስደው በንግድ ትርዒቱ ላይ ተሳታፊ የሆኑ ኩባንያዎችን ስታንድ እየተዘዋወሩ ጎብኝተዋል፡፡
ሆርቲካልቸርን በሚመለከት የመንግሥት መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በደጋው አካባቢና ለዋና ዋና ከተሞች ቅርብ በሆኑ አካባቢዎች የሚካሄደው የግል ኢንቨስትመንት ትኩረት በውስን መሬት ላይ ሰፊ ጉልበት በመጠቀም ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን የሆርቲካልቸር ምርቶች ማምረት የሚቻል መሆኑን ነው፡፡
ይህ ዓይነቱ የግል ባለሀብት የግብርና ልማት ከፍተኛ የመሠረተ ልማትና ጉልበት አቅርቦት የሚጠይቅ ነው፡፡ የግብርና ልማቱ ከአርሶ አደሩ ግብርና ጋር እየተቀናጀ ሊካሄድ የሚችል በተነፃፃሪ መለስተኛ ካፒታል የሚጠይቅ በመሆኑ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በስፋት ሊሳተፉበት የሚችልና እንዲሳተፉም የሚበረታታበት እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡
የሆርቲካልቸር ልማት ግቦች የሚሆኑት የሆርቲካልቸር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በተፋጠነና ቀጣይነት ባለው መልኩ ልማቱ እንዲስፋፋ ማድረግና በሒደት የኢትዮጵያ ባለሀብት ተሳትፎ የጎላ እንዲሆን ማስቻል መሆኑንም እቅዱ ያሳያል፡፡ ከዚህም ሌላ የጥራት ደረጃቸው የተጠበቀና ዓለም አቀፍ የደህንነት መስፈርቶችን ያሟሉ ተወዳዳሪዎች የሆርቲካልቸር ምርቶች በብዛትና በጥራት እንዲሁም በዓይነት ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ ማመቻቸትና ለሆርቲካልቸር ኢንዱስትሪ ልማት ድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶችና ኢንዱስትሪዎች የሚስፋፉበት ሁኔታ ማመቻቸት ይሆናል፡፡
በሆርቲካልቸር ኤክስፖርት ልማት ኢንቨስትመንት በማፍሰስ ዙርያ ሊቀርቡ የሚችሉ የመሬት አቅርቦትን በተመለከተም ልማቱ እንዲስፋፋና እንዲፋጠን በተመረጡ አካባቢዎች የተጀመረውን የእርሻዎች ስብስብን ማጠናከርና አዳዲስ ስብስብን ለመፍጠር የሚያስችል መሬት ተለይቶ በመሬት ባንክ መልክ መያዝ አንዱ መፍትሔ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በአዲስ አበባ ዙርያ የተፈጠረውን የእርሻ ስብስብ የማስፋፋትና የማጠናከር ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች ዙርያም እንደአመቺነቱ ተመሳሳይ ስብስቦች እንዲፈጠሩ እርስ በራሳቸው እንዲደጋገፉና እንዲመጋገቡ የማድረግ ሥራ ይሠራል፡፡ ለዘርፉ የሚሆን የሠለጠነ የሰው ኃይል ለማዘጋጀት የሚያስችለውን የሆርቲካልቸር ተግባራዊ ማሰልጠኛ ማዕከላት የተለያዩ ሥነ ምህዳሮችን ሊወክሉ በሚችሉ ቦታዎች የማደራጀት፣ ለሆርቲካልቸር የኤከስፖርት ልማት የሚፈለገውን የኢንቨስትመንት ወጪ ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎች ይሠራሉ የሚል እቅድ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በዚህ ለእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሠረት በቀጣይ አምስት ዓመት በአበባ የሚሸፈን መሬት አሁን ካለበት 1,586 ሔክታር ወደ 3,000 ሔክታር እንዲያድግ ይሆናል፡፡ የአበባ ምርት አሁን ካለበት 2.74 ቢሊዮን ዘንግ ወደ 5.86 ቢሊዮን ዘንግ ያድጋል፡፡ በአትክልት፣ ፍራፍሬና ኸርብስ አሁን ተሸፍኖ ከሚገኘው 2,472 ሔክታር ወደ 33,000 ሔክታር እንዲያድግ ይደረጋል፡፡ በምርት ረገድ አሁን ከሚገኝበት 58,400 ቶን ወደ 979,600 ቶን እንዲያድግ ይደረጋል የሚል ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከ90 በላይ በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ የተሰማሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላዩ የውጭ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ከአሥር ዓመት በፊት በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች ከአሥር አይበልጡም ነበር፡፡
0 comentários:
አስተያየት ይለጥፉ