መቅደላ
መቅደላ ወይም በአሁኑ ስሙ አምባ ማርያም የሚባለው አምባ፣ ወሎ ውስጥ የሚገኝ በአጼ ቴወድሮስ ዘመን ለዋና ከተማነት ታጭቶ በመካከሉ በእንግሊዞች ጦርነት ወቅት የተቃጠለ ከተማ ነው። በአሁኑ ወቅት በአካባቢው 1899 ሰወች ይኖራሉ።
መቅደላ አምባ እና ዓፄ ቴዎድሮስ
መቅደላ አምባ ለመድረስ ከደሴ ከተማ በስተምዕራብ ፻፳፰ ኪ/ሜ ርቀት ላይ ከምትገኘው የተንታ ከተማ በስተሰሜን ምስራብ ፳፱ ኪ/ሜ መጓዝን ይጠይቃል፡፡ ጥንት ከመቅደላ ደብረ ታቦር ከዚያም ወደጣና ሐይቅ ዳርቻ የሚያዘልቅ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ጐብኝዎች የሚታወቅ የእግር መንግድ ነበር፡፡ ግን ልክ እንደ ጥንታዊው የላሊበላ ሰቆጣ መንገድ ሁሉ መስመሩ ከተዘጋ ዘመናት ተቆጥረዋል።
መቅደላ ሲነሳ ዓፄ ቴዎድሮስ መታወሳቸው የማይቀር ነው፡፡ የመቅደላ አምባ ዙሪያ ገባውን ከርቀት ለመቆጣጠር የሚያስችል በመሆኑና በዘመኑ የፖለቲካ ከርሰ-ምድር ሁነኛ ሥፍራ ላይ በመገኘቱ ከፍተኛ ቁልፋዊ ጥቅም ነበረው፡፡ ይህ ጠቀሜታ ደግሞ በወቅቱ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ለሚጥር ንጉሥና ባለሟሎቹ የሚሰወር አልነበረም።
በንጉሠ ነገሥቱ የፖለቲካ ሥልጣን መባቻ ለሰባት ወራት የተካሄደው የወሎ ዘመቻ የተጠናቀቀውም በመቅደላ መያዝ ነበር፡፡ ዓፄ ቴዎድሮስ ከጎንደር በኋላ የሥልጣን ማእከላቸውን ለጊዜው ወደ ደብረ ታቦር ከዚያም ወደመቅደላ በማዞር ለተቀረው ግዛት ዓርዓያ ሊሆን የሚችል የአስተዳደር ሥርዓት ለማቆም ጥረት የጀመሩት በዚሁ ሥፍራ ነበር፡፡ በርካታና የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች፣ ብዛት ያላቸው ገድሎች፣ መጻሕፍትና ድርሳናት እንዲሁም የንጉሠ ነገሥቱ የግል የክብር ዕቃዎች በሥርዓት ተሰድረው ይቀመጡ የነበረው በመቅደላ ግምጃ ቤት ነበር።
በዘመኑ ፲፭ መድፎች፣ ፯ ሞርታሮች፣ ፲፩ ሺ ፷፫ የተለያዩ ጠመንጃዎች፣ ፰፻፸፭ ሽጉጦችና ፬፻፹፩ ሳንጃዎች፣ ፭፻፶፭ የመድፍና የሞርታር አረሮች እንዲሁም ፹፫ ሺ ፭፻፷፫ የተለያዩ ጥይቶች በመቅደላው ግምጃ ቤት እንደነበሩ መረጃዎች ይገልፃሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ለታሪክ መዘክርነት በቦታው ከሚገኙት ቅርሶች አንዱ ‘ሴባስቶፖል’ የተባለው የንጉሠ ነገሥቱ ትልቅ መድፍ እና ዓፄ ቴዎድሮስ ጊዜያዊ ቤተ መንግሥት ፍርስራሽና የመቃብር ቦታዎች ናቸው፡፡ መጽሐፍቱ፣ ድርሳናቱ፣ የወርቅና ብር ዋንጫዎች፣ አክሊሎችና ሌሎች የንጉሠ ነገሥቱ የግል ሀብቶች የነበሩ ቅርሶች ሁሉ ከመቅደላው ጦርነትና ከዓፄ ቴዎድሮስ እረፍት በኋላ በደላንታ ሜዳ ለጨረታ ተሰጥተው በ ናፒዬር የተመራው የእንግሊዝ ሠራዊት ተቀራምቷቸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ከንጉሠ ነገሥቱ አናት ላይ የተሸለተውን ሹሩባ ፀጉር ጨምሮ ሌሎች ቅርሶች በእንግሊዝ አገር የተለያዩ የሥነ-ቅርስ መዘክሮች ውስጥ ተቀምጠው ይገኛሉ።
ከዓርዓያዊ የአስተዳደር ማዕከልነትና ግምጃ ቤትነት ባሻገር የንጉሠ ነገሥቱ ወህኒ ቤትም የሚገኘው በመቅደላ ነበር፡፡ በእጅ ተይዘው በሞት ያልተቀጡ ጠንካራ የሥልጣን ተቀናቃኞች፣ ምርኮኞችና አማጽያን ከመቅደላ ነዋሪዎች ጥቂቶቹ ነበሩ። ከእነዚህም አንዱ የኋላው ንጉሠ ነገሥት የያኔው ደጃዝማች ምኒሊክ ናቸው። ምኒልክ ለ አሥራ አንድ ዓመታት የመቅደላ እስረኛ ነበሩ። አጼ ቴዎድሮስ ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር በነበራቸው ጠብ እልህ ውስጥ ገብተው በጎንደር ይኖሩ የነበሩ የውጭ ዜጎችን ሰብስበው ያጎሩት በመቅደላው ወህኒ ቤት ነበር፡፡ በመጨረሻም የመቅደላ አምባ የአጼ ቴዎድሮስ ሥልጣን መደላደል ምልክት የመሆኑን ያህል የፍጻሜያቸውም ተምሳሌት ሆኗል።
ሁሉም ነገር አብቅቶ የማይቀረው ፍፃሜ ሲቀርብ ራሳቸውን በክብር ያጠፉት በዚሁ በቅደላ አምባ ነው፡፡ የመቅደላ አምባ ከአጼ ቴዎድሮስ ሞት በኋላም እስረኞች የሚታገቱበት ሥፍራ መሆኑ አልቀረም። ከሰገሌ ጦርነት አምስት ዓመት ቀደም ብሎ በታኅሣሥ ወር ፲፱፻፫ ዓ/ም የወሎው ራስ ሚካኤል አልጋ ወራሽነት ታጭተው የነበሩትን የልጃቸውን የልጅ ኢያሱን ሥልጣን ለማጠናከርና ሁኔታዎችን ለመቆጣጠር ወደ ስምንት ሺህ የሚደርስ የወሎ ሠራዊትን አስከትለው ወደ አዲስ አበባ ከዘመቱ በኋላ ይደርሳል ተብሎ የተፈራው ግጭት በአቡኑ እና በእጨጌው ገላጋይነት በርዶ ራስ ሚካኤል ወደ ወሎ ሲመለሱ ከአመጹት መካከል አንዱ ናቸው ያሏቸውን ራስ አባተ ቧ ያለውን ወደ መቅደላ በመውሰድ ለአምሥት ዓመታት በእስር አቆይተዋቸዋል፡፡ ከሰገሌ ጦርነትም በኋላ ልጅ ኢያሱ እራሳቸው ከማዕከላዊው መንግሥት በሸሹበት ጊዜ እዚሁ መቅደላ ላይ ለጥቂት ጊዜ መሽገው እንደነበር ታሪክ ይዘግባል።
ታሪኩን ለሚያውቅ የመቅደላ ጉብኝት ልዩ ስሜት ይፈጥርበታል፡፡ ሁሉም ጐብኝ ግን የቴዎድሮስን ፍፃሜ በዓይነ ህሊናው ማስተዋሉ አይቀርም፡፡ በመቅደላ አምባ አካባቢ ሊጐበኙ ከሚችሉ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶች መካከል በ፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአብርሐ ወአጽብሐ ዘመነ መንግሥት መተከሉ የሚነገርለት የሰላምጌ ሥላሴ፣ በአጼ ላሊበላ ዘመን ከአንድ አለት ተፈልፍሎ የተሠራው የፉል አምባ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፣ በ፲፭ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዓፄ ይስሐቅ ዘመነ መንግሥት መመሥረቷ የሚታመነው የመቅደላ ማርያምና በ፳ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በንጉሥ ሚካኤል የተሠራው የተንታ ሚካኤል አብያተ ክርስቲያናት ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በውስጣቸውም የኢትዮጵያን ጥንታዊነት የሚዘክሩና በርካታ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን ይዘዋል።
0 comentários:
አስተያየት ይለጥፉ