የትግራይና የአማራ ክልል ተራራማ አካባቢዎች በጠረጴዛ እርከን እየለሙ ነው

 
የትግራይና የአማራ ክልል ተራራማ አካባቢዎች በጠረጴዛ እርከን እየለሙ ነው

የትግራይና የአማራ ክልል ተራራማ አካባቢዎች በጠረጴዛ እርከን እየለሙ ነው

አዲስ አበባ ሐምሌ 19/2006 የትግራይና የአማራ ክልል ተራራማ አካባቢዎች የጠረጴዛ እርከን ቴክኖሎጂን በመጠቀም በስፋት እየለሙ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ ከፍተኛ የተፋሰስ ልማት ባለሙያ አቶ ኃይለሚካኤል አየለ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ተራሮችን ቆርጦ በተለያዩ የድንጋይ ካብ በመስራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በስፋት እየተሰራ ይገኛል።

በእርከን ስራው በአዲስ መልክ የሚለሙ ተራራማና ተዳፋት መሬቶች መፈጠራቸውንና ከዚህ በፊት ለልማት የማይሆን መሬት በቴክኖሎጂው አማካኝነት ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል።

"የጠረጴዛ እርከንን በተራራማ መሬቶች ላይ በመስራት የህብረተሰቡን ህይወት ከመቀየርና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማሳደግ ረገድ ቴክኖሎጂው ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል" ነው ያሉት።

በገጠር የስራ እድል ፈጠራን ታሳቢ በማድረግና ባለው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል እንዲሁም ሊለማ የሚችል ሰፊ ተራራማ የመሬት ኃብትና ቴክኖሎጂው በአጭር ጊዜ የሚያስገኘው ውጤት ታሳቢ ተደርጎ ስራው እንደሚከናወን ተናግረዋል።

ቴክኖሎጂው የመሬቱ ተዳፋትነት ከ12 እስከ 58 በመቶ በሆነ፣ የአፈር ጥልቀቱ በተሻለ፣ የድንጋይ አቅርቦት አማራጭ ባለበትና የደን ሽፋኑ አናሳ በሆነ አካባቢ ተግባራዊ ይደረጋል።

በጠረጴዛ እርከን አማካኝነት አዲስ በተፈጠረው መሬት ላይ የጓሮ አትክልቶችና የተለያዩ ተክሎች እንደሚለሙ ባለሙያው አስረድተዋል።

ስራው ከሁለት ዓመታት በፊት በሰሜን ወሎ ወቄት ወረዳ በዘመናዊ መንገድ የተጀመረ ሲሆን የትግራይና የአማራ ክልሎች ሞዴል በመቀመርና በስልጠና በማሻሻል ተግባራዊ እያደረጉት ይገኛሉ።

ክልሎቹ የመሬት አቀማመጣቸው ተራራማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቴክኖሎጂውን ከሌሎች ዘዴዎች ጋር በማቀናጀት ስራ ላይ እንዲውል አድርገዋል።

በግብርናው መስክ የታየውን እድገት ለማፋጠንና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ መንግስት ከነደፋቸው ስትራቴጂዎች አንዱ የሆነውን ይህን ዘዴን በመቀመር ወደ ሌሎች ተራራማ አካባቢዎች ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን አቶ ኃይለሚካኤል ተናግረዋል።

ከድንጋይ ካብ በተጨማሪ በአፈር የሚሰራባቸው የውጭ ልምዶችን ከቻይና፣ ከኮሪያና ከሩዋንዳ በመውሰድ ለክልሎች ለማድረስ ሚኒስቴሩ በሂደት ላይ እንደሚገኝም ነው የገለጹት።

በዚህ ዘዴ በሁለት አመታት ጊዜ ውስጥ በትግራይና በአማራ ክልሎች ሰፊ መሬት መልማቱን ባለሙያው ይናገራሉ።

በትግራይ እንዳመሆኒ ወረዳ ብቻ 300 ወጣቶች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ሴቶች ናቸው።

የልቅ መሬት ግጦሽን ማስቀረት አለመቻል፣ አርሶ አደሩ ተራራማ መሬትን ለልማት ለመስጠት ፍቃደኛ ያለመሆንና ከጥራት ጋር ተያይዞ የተገነቡ ካቦች መፍረስ እንደችግር ያጋጠሙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የቻይናውያን ፈጠራ እንደሆነ የሚነገርለትና ተራራማ በሆኑት አገራት የሚዘወተረው የጠረጴዛ እርከን በአብዛኞቹ የምስራቅ አፍሪካ አገራትና በደቡብ አፍሪካ በስፋት እየተለመደ መጥቷል።

ከ400 ዓመታት በፊትም በኮንሶ በባህላዊ መንገድ ይሰራበት እንደነበር ይታወሳል። 

አንተ ይፈልጋሉ? አጋራ:

ተዛማጅ ልጥፎች