ሠፈሮች
የአዲስ አበባ ከተማ ሠፈሮች ስያሜያቸውን ያገኙት በተለያዩ ምክንያቶችና አጋጣሚዎች ነው። እነዚህንም በተለያዩ ዘርፎች ከፍሎ በቅደም ተከተል ማየት ይቻላል።
በርካታዎቹ የከተማዋ ቀደምት ሠፈሮች ስያሜያቸውን ያገኙት በቤተ-መንግሥቱ ዙሪያ መሬት በጉልት መልክ በተሠጣቸው መሣፍንቶችና መኳንንቶች ስም ነው። በዚህ መልክ ስያሜያቸውን ካገኙት ሠፈሮች መካከል ራስ መኮንን ሠፈር፣ ራስ ተሰማ ሠፈር፣ ራስ ብሩ ሠፈር፣ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ሠፈር፣ ራስ ስዩም ሠፈር፣ ደጃዝማች ውቤ ሠፈር፣ ነጋድራስ ኃይለ ጊዮርጊስ ሠፈር ፣ ደጃዝማች ዘውዱ አባኮራን ሠፈር እና ሸጎሌ (የአሶሣ ገዢ በነበሩት በሼክ ሆጀሌ አል ሐሠን የተሠየመው) ሠፈር ይጠቀሳሉ።
ከእነዚህ ሠፈሮች መካከል ደጃዝማች ውቤ ሠፈር በተለይ ከጣሊያን ወረራ በፊት በሴተኛ አዳሪነት የሚተዳደሩ ነዋሪዎች በከፍተኛ ደረጃ ከሚገኙባቸው የከተማዋ ሠፈሮች አንዱ እንደነበረ ይነገራል። በዚህም ሳቢያ በስነ ቃል በርካታ ግጥሞች በዚህ ሠፈር ዙሪያ ተገጥመዋል። ከነዚህም መካከል፣
«ደጃች ውቤ ሠፈር ምን ሠፈር ሆነች፣
ያችም ልጅ አገባች ያችም ልጅ ታጨች።
ደጃች ውቤ ሠፈር ሲጣሉ እወዳለሁ፣
ገላጋይ መስዬ እገሊትን አያለሁ።
ደጃች ውቤ ሠፈር የሚሠራው ሥራ፣
ጠይሟን በጥፊ ቀይዋን በከዘራ»
የሚሉት ይገኙበታል።
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከመላው የአገሪቱ ማዕዘናት መጥተው አዲስ አበባ በሠፈሩ ብሔረሰቦች የተመሠረቱ ሠፈሮች ይጠቀሳሉ። በዚህ መልክ ከተመሠረቱት ሠፈሮች መካከል ለአብነት አደሬ ሠፈር፣ ጎፋ ሠፈር፣ ወሎ ሠፈር፣ ወርጂ ሠፈር፣ መንዜ ሠፈርና ሱማሌ ተራ ይገኙበታል። የወርጂ ሠፈርን የመሠረቱት የወርጂ ብሔረሰብ አባላት በቆዳና በበርኖስ ንግድ የተሠማሩ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል። በተመሣሣይ መልኩ የሱማሌ ተራ ነዋሪዎች ዋነኛ መተዳደሪያ የሻይ ቤት ሥራ እንደነበር ይታመናል።
በሶስተኛ ደረጃ በተለያዩ ሙያዎች ተሠማርተው በተለይም በቤተ መንግሥቱ የተለያዩ የሥራ ድርሻዎች በነበራቸው ባለሙያዎች የተቆረቆሩ ሠፈሮችን እናገኛለን። እነዚህም ከብዙ በጥቂቱ ሠራተኛ ሠፈር፣ ዘበኛ ሠፈር፣ ሥጋ ቤት ሠፈር፣ ኩባንያ ሠፈር፣ ጠመንጃ ያዥ ሠፈር፣ ካህን ሠፈር (በኋላ ገዳም ሠፈር) ፣ ገባር ሠፈር ፣ ሠረገላ ሳቢ ሠፈርና ውሃ ስንቁ ሠፈርን ያካትታሉ። ሠራተኛ ሠፈር በአፄ ምኒልክ ቤተ-መንግሥት በዕደ ጥበባት ሙያ በተሠማሩ ነዋሪዎች የተመሠረተ ሠፈር ነው። የሠፈሩ መሥራቾች ዋነኛ ሙያ የብረታ ብረት ሥራ እንደነበረ ይነገራል። ይሄም የተለያዩ የብረታ ብረት ውጤቶችን ለምሣሌ ማረሻ፣ የፈረስ እርካብን፣ የቤት እቃዎችን፣ የጋሻና ጦር እና የጠመንጃ ዕድሳትን ይጨምራል። በቤተ መንግሥቱ በአናጢነት የተሠማሩ ባለሙያዎችም የሚኖሩት በሠራተኛ ሠፈር እንደነበር ይነገራል።
በከተማዋ ከሚኖሩት የውጭ ተወላጆችም መካከል ጥቂቶቹ የሚኖሩት በዚሁ ሠፈር ነበር። ከነዚህም የውጭ ነዋሪዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት አርመናዊው የግብረ ህንፃ ባለሙያ ሙሴ ሚናስ ሔርቤጊን ነበሩ። ዘበኛ ሠፈር የቤተ-መንግሥቱ ጠባቂዎች ወይም የዕልፍኝ ዘበኞች የሠፈሩበት ሠፈር ሲሆን፣ ገባር ሠፈር ደግሞ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍላተ ሀገር እንደ ማር፣ እህልና ከብት በመሣሠሉት ምርቶች ዓመታዊ ግብር ለመክፈል ወደ ከተማዋ በሚመጡ ግለሰቦች የተመሠረተ ሠፈር እንደሆነ ይነገራል። የውሃ ስንቁ ሠፈር መስራቾች ደግሞ መደበኛ ክፍያ የሌላቸው እና ስንቃቸው ውሃ ብቻ የሆነ የጦሩ አባላት የሠፈሩበት ሠፈር እንደነበረ ይነገራል።
በሌላ በኩል ጥቂት የማይባሉ የአዲስ አበባ ሠፈሮች ስያሜያቸውን ያገኙት በተለያዩ አጋጣሚዎች፣ ክስተቶችና ታሪካዊ ክንዋኔዎች ነው። ሠባራ ባቡር ፣ እሪ በከንቱ ፣ ዶሮ ማነቂያ ፣ አፍንጮ በር ፣አራት ኪሎ ፣ ስድስት ኪሎ ፣ አምስት ኪሎ ፣ ጣሊያን ሠፈር፣ ሃያ ሁለት ማዞሪያ፣ ሽሮ ሜዳ እና ነፋስ ስልክ ተብለው የሚጠሩትን ሠፈሮች በዚሁ ዘርፍ መፈረጅ ይቻላል። ሰባራ ባቡር ሠፈር ስያሜውን ያገኘው ሙሴ ሰርኪስ ተርዚያን በሚባሉ አርመናዊ ነጋዴ አማካኝነት ከውጭ አገር መጥቶ አሁን ስያሜውን ባገኘበት ቦታ ተበላሽቶ በቀረው የመንገድ መሥሪያ ተሽከርካሪ (ሮለር) ምክንያት ሠፈሩ ሰባራ ባቡር እንደተባለ ይነገራል። አገሬው “የሠርኪስ ባቡር” እያለ የሚጠራው መሣሪያ አዲስ አበባ በደረሰ ጊዜ የሚከተለው ግጥም ተገጥሞለት ነበር።
«ባቡሩ ሰገረ ስልኩም ተናገረ፣
ምኒልክ መልአክ ነው ልቤ ጠረጠረ።»
በሌላ በኩል ከዐድዋ ጦርነት በኋላ በድል አድራጊው የኢትዮጵያ ሠራዊት የጦር ምርኮኞች የሆኑት የጣሊያን ተወላጆች በማረፊያነት የተመረጠው ቦታ ጣሊያን ሠፈር የሚለውን ስያሜ ማግኘቱ ይታወቃል። እንደዚሁም የስድስት ኪሎ ሠፈር ፣ አራት መንገዶች መገናኛ የሆነው አካባቢ አራት ኪሎ ሠፈር በሁለቱ ሠፈሮች መካከል ያለው አካባቢ ቆይቶ አምስት ኪሎ ሠፈር የሚለውን ስያሜ ማግኘቱም የሚታወቅ ነው።
ሌላው በከተማው ከሚገኙ ዋና ዋና ሠፈሮች መካከል በከተማዋ ቀደምት ነዋሪዎች በሆኑት የኦሮሞ ተወላጆችና የቦታ ስሞች የተሰየሙ ሠፈሮችን እናገኛለን። ከነዚህም መካከል ጉለሌ ፣ ጎርዶሜ ፣ ቀበና ፣ ኮተቤ ፣የካ ፣ እንዲሁም ገርጂ እና ላፍቶ የተባሉት ሠፈሮች ለአብነት ይጠቀሳሉ። ከእነዚህም ሠፈሮች መካከል በቀበና ወንዝ ስም በተሰየመው ቀበና ሠፈር ከተገጠሙት ግጥሞች አንዱን እንመልከት።
«ቀበና ለዋለ አራዳ ብርቁ ነው፣
አራዳም ለዋለ ቀበና ብርቁ ነው፣
እሱስ ላገናኘው ሴት ወይዘሮም ደግ ነው።»
በሌላ ዘርፍ ከ1928 የጣሊያን ወረራ እና የአምስት ዓመት ቆይታ ጊዜ አንዳንድ የአዲስ አበባ ቦታዎች እና ሠፈሮች የጣሊያንኛ ስያሜ አግኝተዋል። ከእነዚህም መካከል መርካቶ (የአገሬው ገበያ) ፣ ፒያሣ (የቀድሞው አራዳ) ፣ ካዛንቺስ፣ ካዛ ፖፖላሬ እና ካምቦሎጆ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ካዛንቺስ ስያሜውን ያገኘው አዲስ አበባ በጣሊያን ይዞታ ስር በነበረችበት ጊዜ ለከፍተኛ የጣሊያን ሹማምንት መኖሪያ ቤቶች በሠራው የጣሊያን ኩባንያ ምህፃረ ቃል ሲሆን ካዛ ፖፖላሬ ደግሞ በዝቅተኛ ደረጃ ለሚገኙ ጣሊያናዊያን ቤቶች በሠራው በካዛ ፖፖላሬ ኩባንያ ስም ነው ስያሜውን ያገኘው። በሌላ በኩል ካምቦሎጆ ሠፈር መጠሪያውን ያገኘው ካምፖ አሎጅዬ ኦፔራ (Campo Allogio Opera) ከሚለው ስም ሲሆን ይሄም ማለት የሠራተኞች ካምፕ ማለት ነው።
እንዲሁም በከተማዋ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያን እና አጥቢያዎች የተሰየሙ ሠፈሮች ሌላው ዋነኛ ዘርፍ ነው። በዚህ ዘርፍ ከሚገኙ ሠፈሮች መካከል ተቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዘው አራዳ ጊዮርጊስ ሠፈር ነው። አራዳ በተለይም ከጣሊያን ወረራ ቀደም ባለው ጊዜ የአዲስ አበባ የኢኮኖሚ ማዕከል ከመሆኑ አኳያና በርካታ ማሕበራዊ ክንዋኔዎችን ያስተናግድ የነበረ ሠፈር እንደመሆኑ በስነቃል ብዙ ተብሎለታል። ለአብነት
«ሱሪ ያለቀበት አይገዛም አዲስ፣
ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ጊዮርጊስ።
እስኪ አራዳ ልውጣ ብርቱካን ባገኝ፣
ትናንት ኮሶ ጠጣሁ ዛሬ መረረኝ።
ምነው በአደረገኝ ከአራዳ ልጅ መሣ፣
እንኳን ለገንዘቡ ለነፍሱ የማይሣሣ።
የአራዳ ዘበኛ ክብሬ ነው ሞገሴ፣
በቸገረኝ ጊዜ የሚደርስ ለነፍሴ» የሚሉት ይገኙባቸዋል።
በዚህ ዘርፍ የሚመደቡ ሌሎች ሠፈሮች ደግሞ አማኑኤል ፣ ዮሴፍ ፣ ኪዳነ ምሕረት ፣ ቀራኒዮ መድኃኔ ዓለም ፣ እና ቀጨኔ መድኃኔ ዓለምን ያካትታሉ። እ.ኤ.አ. ከ 1888 ዓ.ም. የዐድዋ ጦርነት ድል እና ከአዲስ አበባው ስምምነት በኋላ ጣሊያን፣ ሌሎች የአውሮፓ መንግሥታት እና አሜሪካ የአገራችንን ሉዓላዊነት በመቀበል ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሥርተዋል። በዚህ ሂደት በርካታ አገሮች የነዚህን አገሮች ፈለግ በመከተል ኤምባሲዎቻቸውን በአዲስ አበባ ከፍተዋል። ከአዲስ አበባ በርካታ ሠፈሮች መካከል አንዳንዶቹ ስያሜያቸውን ያገኙት ከእነዚህ ኤምባሲዎችና ቀደም ሲል ደግሞ ከሌጋሲዮኖች ነው። ፈረንሣይ ሌጋሲዮንና ሩዋንዳ ሠፈሮች ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው። በመጨረሻም ከአዲስ አበባ ሠፈሮች መካከል አንዳንዶቹ በታዋቂ የውጭ አገር ዜጎች ስም የተሠየሙ ናቸው። ከእነዚህም መካከል ቤኒን ሠፈር እና ተረት ሠፈር ይገኙበታል። ቤኒን ሠፈር ስያሜውን ያገኘው ከጣሊያን ወረራ በፊት ተዋቂ ነጋዴ በሆኑት የአይሁድ ተወላጅ ቤኑን ሲሆን ተረት ሠፈር ደግሞ ስያሜውን ያገኘው በአዲስ አበባ ከተከፈቱት ከመጀመሪያዎቹ ሆቴሎች አንዱ በነበረው በሆቴል ዳፍራንስ ባለቤት በሆኑት ፈረንሣዊው ሙሤ ቴረስ ስም ነው።
አዲስ አበባ (አዲስ ፡ አበባ)
|
0 comentários:
አስተያየት ይለጥፉ