ሶቪዬት ሕብረት

 
ሶቪዬት ሕብረት

ሶቪዬት ሕብረት

ሶቭየት ሕብረት ሰብአዊ ሪፐብሊክ በ፲፱፻፲ ዓ.ም. የተከሰተውን የሩሲያ አብዮት ፍንዳታ፤ እንዲሁም ያንን ተከትሎ ለሦስት ዓመታት የተከናወነውን የሩሲያ «ውስጣዊ ሕዝባዊ የርስ በርስ ግጭት» ተከትሎ በስብአዊ ሕገ መንግሥት (socialist constitution) በአራት ሪፑብሊኮች ቅንብርነት የተመሠረተ አገር ነበር።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ ከቀድሞው የናዚ ጀርመን እጅ የተወሰዱ አገሮችን በማቀላቀል እንዲሁም በ፲፱፻፵፱ ዓ.ም በጉልበት ሌሎች የምሥራቅ አውሮፓ አገሮችን በመቀላቀል ሕብረቱ አሥራ ስድስት ሪፑብሊኮችን ያካተተ ነበር። በዘመን ቆይታና በጥንካሬም የጎለበተ ሕዝባዊ ዓብዮታዊ የሕብረት ሪፑብሊክ በመሆኑም በተለይ በ«ቀዝቃዛ ጦርነት» (cold war) በሚባለው በ«ምዕራብና በምሥራቅ» ዓለም ተከስቶ በነበረው ፍጥጫ ጊዜ፣ በዓለም ላይ ለሚመሠረቱ ሕዝባዊ መንግሥታት ዋና የሽከታ አርአያ የነበረ መንግሥት ነበር።

በ ፲፱፻፵፯ ዓ.ም. የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ፍጻሜ ጀምሮ ይሄ ሕብረት እስከፈረሰበት እስከ ፲፱፻፹፬ ዓ.ም ድረስ በተካሄደው የ«ቀዝቃዛ ጦርነት» ዘመን የሶቪየት ሕብረት በዓለም ከነበሩት ሁለቱ ተቃራኒ ኃያላን መንግሥታት አንዱ ሲሆን፤ በኢትዮጵያም ላይ በ፲፱፻፷፮ ዓ.ም የተመሠረተውን የአብዮት ወታደራዊ የደርግ መንግሥት በጦር መሣሪያ፤ በአማካሪነት፤ በገንዘብ፤ ወዘተረፈ፤ ዋነኛ ደጋፊና ታላቅ ተዋናይ አገር ነበር።

በሕዝባዊ አብዮታዊ እንቅስቃሴ መነሻነት በኃይልና በፖለቲካ ሚዛናት በሰባ ዓመታት ውስጥ ዳብሮ በዓለም ከሁለቱ ኃያላን መንግሥታት አንዱ እስከመሆን የደረሰው የሶቪየት ሕብረት በዕድሜው መግቻ ዓመታት ላይ በዓለም የተከሰቱ ሁለት ዓቢይ ጉዳዮች ለፍጻሜው ዋና ምክንያቶች እንደነበሩ ይገለጻል።

ኬኔዝ ኤስ ዴፊይስ (Kenneth S. Deffeyes) “Beyond Oil” ላይ እንዳሰፈረው አንደኛው፤ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ሮናልድ ሬጋን ሳውዲ አራቢያ የነዳጅ ዋጋዋን እንድታወርድ በማበረታታቸው የሶቪዬት ሕብረት ከነዳጅ ሽያጥ የምታገኘውን ትርፍና የውጭ ምንዛሪ መጠን ክፉኛ ማመንመኑ፤ ሁለተኛ በሶቪዬት ሕብረት ሥልጣንን የተረከቡት ሚካይል ጎርባቾቭ በአገሪቱ ዱኛ (economy) እንዲሁም የኮሙኒስት አመራር ላይ ጥልቅ የሆኑ ፔሬስትሮይካ እና ግላስኖስት በሚል ስያሜ የሚታወቁትን ሁለት ሥር ነቅናቂ ለውጦችን መትግበራቸው ነው።

ለምሳሌ የጎርባቾቭ የግላስኖስት ውጅማ (policy)፣ ከዚህ በፊት በአስተዳደሩ መሣሪያዎች ከሕዝቡ በምስጢርነት ይደበቁ የነበሩ መንግሥታዊ/ሰብአዊ፤ ወ.ዘ.ተ. መረጃዎችን ማንኛውም ዜጋ የማግኘት መብቱን ያረጋገጠለት አቢይ ውጅማ ሲሆን፤ የፔሬስትሮይካ ስልት ደግሞ ከአብዮቱ ጀምሮ የማዕከላዊው የኮሙኒስት ሸንጎ በቁልፍ እጅ ይዞት የነበረውን ስልጣን በማላቀቅ የቻራስፍና (democracy) ስርዐት በሕዝቡ አዕምሮ እንዲሰነጽ መንገድ የከፈተ ውጅማ ነው።

የቀድሞው የሶቪዬት ሕብረት መጨረሻ ላይ ታሕሣሥ ፲፮ ቀን ፲፱፻፹፬ ዓ.ም ተደምስሶ በዓለም መንግሥታት እውቀትና ስምምነት ህጋዊ ወራሽነት የሩሲያ መንግሥት እንደሆነ ታወጀ። ሩሲያም በዚህ መሠረት የቀድሞውን የሶቪዬት ሕብረት የውጭ ዕዳዎች እንዲሁም የውጭ ንብረቶች በፈቃዱ ተቀበለ። በቀድሞው የሶቪዬት ሕብረት ተፈርመው የነበሩም ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንም ሩሲያ መቀበሏን አስታውቃለች።

አንተ ይፈልጋሉ? አጋራ:

ተዛማጅ ልጥፎች