ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ

 
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ <Haile Selassie>

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ

ቀዳማዊ ፡ ዓፄ ፡ ኃይለ ፡ ሥላሴ (ቀ.ኃ.ሥ.) ከጥቅምት ፳፫ ቀን ፲፱፻፳፫ እስከ መስከረም ፪ ቀን ፲፱፻፷፯ ዓ.ም. ፡ የኢትዮጵያ ፡ ንጉሠ ፡ ነገሥት ፡ ነበሩ። ተፈሪ ፡ መኰንን ፡ ሐምሌ ፲፮ ፡ ቀን ፡ ፲፰፻፹፬ ዓ.ም. ፡ ከአባታቸው ፡ ከልዑል ፡ ራስ መኰንን ፡ እና ፡ ከእናታቸው ፡ ከወይዘሮ ፡ የሺ ፡ እመቤት ፡ ኤጀርሳ ፡ ጎሮ ፡ በተባለ ፡ የገጠር ፡ ቀበሌ ፡ ሐረርጌ ፡ ውስጥ ፡ ተወለዱ።

በ፲፰፻፺፱ ፡ የሲዳሞ ፡ አውራጃ ፡ አገረ ፡ ገዥ ፡ ሆኑ። በ፲፱፻፫ ዓ.ም. ፡ የሐረርጌ ፡ አገረ ፡ ገዥ ፡ ሆኑ። የሐረርጌ ፡ አገረ ፡ ገዥ ፡ ሲሆኑ ፣ በጣም ፡ ብዙ ፡ ሺህ ፡ ተከታዮች ፡ ነበሩዋቸውና ፡ ልጅ ፡ እያሱን ፡ ከእንደራሴነት ፡ በኅይል ፡ እንዳያስወጡ ፤ እያሱም ፡ ተፈሪን ፡ ከሐረር ፡ አገረ ፡ ገዥነት ፡ እንዳይሽሯቸው ፡ የሚል ፡ ስምምነት ፡ ተዋዋሉ። ዳሩ ፡ ግን ፡ እያሱ ፡ ሃይማኖታቸውን ፡ ከክርስትና ፡ ወደ ፡ እስልምና ፡ እንደቀየሩ ፡ የሚል ፡ ማስረጃ ፡ ቀረበና ፡ ብዙ ፡ መኳንንትና ፡ ቀሳውስት ፡ ስለዚህ ፡ ኢያሱን ፡ አልወደዱዋቸውም ፡ ነበር። ከዚህም ፡ በላይ ፡ እያሱ ፡ ተፈሪን ፡ ከሐረር ፡ ከአገረ ፡ ገዥነታቸው ፡ ለመሻር ፡ በሞከሩበት ፡ ወቅት ፡ ስምምነታቸው ፡ እንግዲህ ፡ ተሠርዞ ፡ ተፈሪ ፡ ደግሞ ፡ ለወገናቸው ፡ ከስምምነቱ ፡ ተለቅቀው ፡ በዚያን ፡ ጊዜ ፡ እሳቸው ፡ እያሱን ፡ ከእንደራሴነት ፡ አስወጡ። እንግዲህ ፡ በ፲፱፻፱ ፡ ዓ.ም. ፡ መኳንንቱ ፡ ዘውዲቱን ፡ ንግሥተ ፡ ነገሥት ፡ ሆነው ፡ አድርገዋቸው ፡ ተፈሪ ፡ ደግሞ ፡ እንደራሴ ፡ ሆኑ። ከዚህ ፡ ወቅት ፡ ጀምሮ ፡ ተፈሪ ፡ በኢትዮጵያ ፡ ውስጥ ፡ ባለሙሉ ፡ ሥልጣን ፡ ነበሩ። በመስከረም ፳፯ ፡ ቀን ፡ ፲፱፻፳፩ ፡ ዓ.ም. ፡ የንጉሥነት ፡ ማዕረግ ፡ ተጨመረላችው። በ፲፱፻፳፪ ዓ.ም ፡ ንግሥት ፡ ዘውዲቱ ፡ አርፈው ፡ ንጉሠ ፡ ነገሥት ፡ ሆኑና ፡ ጥቅምት ፳፫ ፡ ቀን ፡ ፲፱፻፳፫ ዓ.ም. ፡ ብዙ ፡ የውጭ ፡ ልዑካን ፡ በተገኙበት ፡ ታላቅ ፡ ሥነ-ሥርዓት ፡ ቅብዓ ፡ ቅዱስ ፡ ተቀብተው ፡ እሳቸውና ፡ ሚስታቸው ፡ እቴጌ ፡ መነን ፡ ዘውድ ፡ ጫኑ።

ቀዳማዊ ፡ ዓፄ ፡ ኃይለ ፡ ሥላሴ ፤ ንጉሠ-ነገሥት ፲፱፻፳፫ - ፲፱፻፷፮

በንግሥ ፡ በዓሉ ፡ ዋዜማ ፡ ጥቅምት ፳፪ ፡ ቀን ፡ የትልቁ ፡ ንጉሠ-ነገሥት ፡ የዳግማዊ ፡ ዓፄ ፡ ምኒልክ ፡ ሐውልት ፡ በመናገሻ ፡ ቅዱስ ፡ ጊዮርጊስ ፡ ቤተ-ክርስቲያን ፡ አጠገብ ፤ ለዘውድ ፡ በዓል ፡ የመጡት ፡ እንግዶች ፡ በተገኙበት ፡ ሥርዐት ፣ የሐውልቱን ፡ መጋረጃ ፡ የመግለጥ ፡ ክብር ለብሪታንያ ፡ ንጉሥ ፡ ወኪል ፡ ለ(ዱክ ፡ ኦፍ ፡ ግሎስተር) ፡ ተሰጥቶ ፡ ሐውልቱ ፡ ተመረቀ።

ለንግሥ ፡ ስርዐቱ ፡ ጥሪ ፡ የተደረገላቸው ፡ የውጭ ፡ አገር ፡ ልኡካን ፡ ከየአገራቸው ፡ ጋዜጠኞች ፡ ጋር ፡ ከጥቅምት ፰ ፡ ቀን ፡ ጀምሮ ፡ በየተራ ፡ ወደ ፡ አዲስ ፡ አበባ ፡ ገብተው ፡ ስለነበር ፡ ሥርዓቱ ፡ በዓለም ፡ ዜና ፡ ማሰራጫ ፡ በየአገሩ ፡ ታይቶ ፡ ነበር። በተለይም ፡ በብሪታንያ ፡ ቅኝ ፡ ግዛት ፡ በጃማይካ ፡ አንዳንድ ፡ ድሀ ፡ ጥቁር ፡ ሕዝቦች ፡ ስለ ፡ ማዕረጋቸው ፡ ተረድተው ፡ የተመለሰ ፡ መሢህ ፡ ነው ፡ ብለው ፡ ይሰብኩ ፡ ጀመር። እንደዚህ ፡ የሚሉት ፡ ሰዎች ፡ እስከ ፡ ዛሬ ፡ ድረስ ፡ ስለ ፡ ፊተኛው ፡ ስማቸው ፡ «ራስ ፡ ተፈሪ» ፡ ትዝታ ፡ ራሳቸውን ፡ «ራስታፋራይ» ፡ (ራሰተፈሪያውያን) ፡ ብለዋል።

ዓጼ ፡ ኃይለ ፡ ሥላሴ ፡ ዘውድ ፡ እንደጫኑ ፡ የአገሪቱን ፡ የመጀመሪያ ፡ ሕገ-መንግሥት ፡ እንዲዘጋጅ ፡ አዝዘው ፡ በዘውዱ ፡ አንደኛ ፡ ዓመት ፡ በዓል ፡ ጥቅምት ፳፫ ፡ ቀን ፡ ፲፱፻፳፬ ፡ ዓ.ም. ፡ በአዲሱ ፡ ምክር ፡ ቤት ፡ (ፓርላማ) ፡ ለሕዝብ ፡ ቀረበ። ከዚህም ፡ በላይ ፡ ብዙ ፡ የቴክኖዎሎጂ ፡ ስራዎችና ፡ መሻሻያዎች ፡ ወደ ፡ ኢትዮጵያ ፡ ከውጭ ፡ አገር ፡ አስገቡ።

በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. ፡ የሙሶሊኒ ፡ ፋሺስት ፡ ሠራዊት ፡ ኢትዮጵያን ፡ በወረረ ፡ ጊዜ ፡ ጃንሆይ ፡ በቆራጥነት ፡ ከታገሉ ፡ በኋላ ፡ የጠላቱ ፡ ጦር ፡ ኅይል ፡ ግን ፡ በመጨረሻ ፡ ወደ ፡ እንግሊዝ ፡ አገር ፡ ለጊዜው ፡ አሰደዳቸው። ወደ ፡ ጄኔቭ ፡ ስዊስ ፡ ወደ ፡ ዓለም ፡ መንግሥታት ፡ ማኅበር ፡ ሄደው ፡ ስለ ፡ ጣልያኖች ፡ የዓለምን ፡ እርዳታ ፡ በመጠየቅ ፡ ተናገሩ። የዓለም ፡ መንግሥታት ፡ ግን ፡ ብዙ ፡ አላደረጉም። በ፲፱፻፴፪ ዓ.ም. ፡ ግን ፡ አውሮፓ ፡ ሁሉ ፡ በሁለተኛው ፡ የዓለም ፡ ጦርነት ፡ ተያዘ። የእንግሊዝ ፡ ሠራዊቶች ፡ ለኢትዮጵያ ፡ አርበኞች ፡ እርዳታ ፡ በመስጠት ፡ ጣልያኖች ፡ ተሸንፈው ፡ በ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ፡ ኢትዮጵያን ፡ ተዉ። ዓፄ ፡ ኃይለ ፡ ሥላሴ ፡ አዲስ ፡ አበባን ፡ እንደገና ፡ የገቡበት ፡ ቀን ፡ ከወጡበት ፡ ቀን ፡ በልኩ ፡ ዕለት ፡ አምስት ፡ ዓመት ፡ በኋላ ፡ ነበረ።

ልጅ ፡ ተፈሪ ፡ መኮንን ፡ በ፲፰፻፺፪ ዓ.ም.

ከዚህ ፡ በኋላ ፡ በ1948 ዓ.ም. ተሻሽሎ የወጣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ፡ የሕዝቦችን ፡ መብቶችና ፡ ተከፋይነት ፡ በመንግሥት ፡ አስፋፍቶ ፡ ሁለቱ ፡ ምክር ፡ ቤቶች ፡ እንደመረጡ ፡ አደረገ። በ፲፱፻፶፭ ዓ.ም. ፡ ግርማዊነታቸው ፡ የአፍሪካ ፡ አንድነት ፡ ድርጅት ፡ በአዲስ ፡ አበባ ፡ እንዲመሠረት ፡ ብዙ ፡ ድጋፍ ፡ ሰጡ። በ፲፱፻፶፰ ዓ.ም. ፡ ወደ ፡ ካሪቢያን ፡ ጉብኝት ፡ አድርገው ፡ የጃማይካ ፡ ራስታዎች ፡ ተገኛኙ። በ፲፱፻፷፯ ዓ.ም. ፡ በማርክሲስት ፡ አብዮት ፡ ደርግ ፡ ሥልጣን ፡ ያዙና ፡ እሳቸው ፡ በእሥር ፡ ቤት ፡ ታሰሩ። በሚከተለው ፡ ዓመት ፡ ከተፈጥሮ ፡ ጠንቅ ፡ እንደ ፡ አረፉ ፡ አሉ ፤ ሆኖም ፡ ለምን ፡ እንደ ፡ ሞቱ ፡ ስለሚለው ፡ ጥያቄ ፡ ትንሽ ፡ ክርክር ፡ አለ። ብዙ ፡ ራስታዎች ፡ ደግሞ ፡ አሁን ፡ እንደሚኖሩ ፡ ይላሉ።

ስያሜያቸው

የዓፄ ፡ ኃይለ ፡ ሥላሴ ፡ የትውልድ ፡ ስም ፡ ልጅ ፡ ተፈሪ ፡ መኮንን ፡ ነው። ስመ-መንግሥታቸው ፡ ግርማዊ ፡ ቀዳማዊ ፡ ዓፄ ፡ ኃይለ ፡ ሥላሴ ፡ ንጉሠ ፡ ነገሥት ፡ ዘኢትዮጵያ ፡ ነበር። ሞዓ ፡ አንበሣ ፡ ዘእምነገደ ፡ ይሁዳ ፡ ሥዩመ ፡ እግዚአብሔር ፡ ንጉሠ ፡ ነገሥት ፡ ዘኢትዮጵያ ፡ የሚለው ፡ የሰሎሞናዊ ፡ ሥረወ-መንግሥት ፡ ነገሥታት ፡ መጠሪያም ፡ በንጉሠ-ነገሥቱ ፡ አርማ ፡ እና ፡ ሌሎች ፡ ይፋዊ ፡ ጽሑፎች ፡ ላይ ፡ ከመደበኛው ፡ ማዕረግ ፡ ጋር ፡ ይጠቀስ ፡ ነበር። ጃንሆይ ፣ ታላቁ ፡ መሪ ፡ እና ፡ አባ ፡ ጠቅል ፡ በመባልም ፡ ይታወቁ ፡ ነበር።

አንተ ይፈልጋሉ? አጋራ:

ተዛማጅ ልጥፎች